Fana: At a Speed of Life!

ክንደ ነበልባሉ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የደህንነት ደጀን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ የሕዝቧን ደህንነትና ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ አለኝታ የሆነ ተቋም ነው።

 

በመደመር መንግሥት ሰራዊቱን ዘመኑን የዋጀ ለማድረግ የተካሄደው አጠቃላይ የመዋቅር፣ የሰው ኃይልና የትጥቅ ሪፎርም ተቋሙን ወደ አዲስ የስኬትና የጥንካሬ ማማ ላይ አድርሶታል::

 

የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የድንበር ወሰን ለማስከበር የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ብቃት ለመወጣት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

 

በሰላም ማስከበር ሥራዎችና ለሕዝብ የደህንነት ስጋቶች ፈጣንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ያረጋገጠ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ቁመናን የተላበሰ ሰራዊት ነው፡፡

 

የመከላከያ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል ብቃት፣ በቴክኖሎጂና በውጊያ ዝግጁነት ደረጃ አዳዲስ ምዕራፎችን ተሻግሯል።

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ ቀዳሚ ድርሻ አለው።

 

የቀጣናውን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሚዛን በሚጠብቅ መልኩ ጥንካሬውን እየገነባ ያለ ተቋም ሲሆን፥ የሀገርን ሕልውና ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና መጫወቱን ቀጥሏል።

 

የጽንፈኛውን አልሸባብ ቡድን ስጋት ለመቀነስና የሶማሊያን መንግሥታዊ ተቋማት ለማጠናከር በተደረገው ዘመቻ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ቀጣናዊ ስጋትን በመመከት ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

 

በተመሳሳይ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል በነበረው ግጭት ወቅት በአብዬ ግዛት ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ሰራዊት ያቀፈው የሰላም ማስከበር ኃይል መሰማራቱም ይታወሳል።

 

በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ደም መፋሰስ በማስቀረት ረገድ የነበረው ሚና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን አድናቆት ያተረፈ ነው።

 

በሩዋንዳና ቡሩንዲ በነበሩት የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወቅት የዜጎችን ሕይወት በመታደግ ረገድ ባከናወነው የሰላም ማስከበር ዘመቻ የሚወደስ ሰራዊት ነው፡፡

 

በአሁኑ ሰዓትም የመከላከያ ሰራዊቱ ድንበር ተሻጋሪ ሽብርተኝነትን፣ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በመከላከል ረገድ የጋራ ቀጣናዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ ቀን ከሌት በተጠንቀቅ በመቆም በደጀንነቱ ቀጥሏል።

 

ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበር፤ የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፣ የጋራ የድንበር ጥበቃና የስልጠና ፕሮግራሞችን ማካሄድ የሰራዊቱ የዘወትር ተግባር ነው።

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለቀጣናው ሰላም ያለው ቁርጠኝነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፤ ለዚህም ባለፉት ዓመታት በተግባር ያከናወናቸው ሥራዎች ምስክር ናቸው፡፡

 

ሰራዊቱ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ለሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር፤ ለኢኮኖሚ ትስስርና ለልማት የተመቸ አስተማማኝ ቀጣና እንዲሆን የሰላምና የመረጋጋት ዋስትና ሆኖ ዘመንን ተሻግሯል።

 

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.