የውጫሌ ከተማ መንገድ በመበላሸቱ ህብረተሰቡና አሽከርካሪዎች መቸገራቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በደቡብ ውሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የውጫሌ ከተማ መግቢያ ድልድይ ላይ አሸባሪው ህወሃት ያደረሰውን ውድመት ተከትሎ የተሰራው ተለዋጭ መንገድ በመበላሸቱ መቸገራቸውን ህብረተሰቡና አሽከርካሪዎች ገለጹ።
በመንገዱ ብልሽት ከውጫሌ ወደ ደሴ ወይም ከደሴ ወደ ውጫሌና ወልዲያ የሚደረግ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ከዛሬ ጧት ጀምሮ በመስተጓጎሉ በርካታ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች መቸገራቸው ተመላክቷል።
አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች እንደገለጹት፥ የተሰራው ተለዋጭ መንገድ ጠባብ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለብልሽት ሲዳረግ ቆይቷል።
ዛሬ መንገዱ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ ለአስቸኳይ ስራ ከሰሜን ወሎ ወደ ደሴም ሆነ ወደ አዲስ አበባ መጓጓዝ እንዳልቻሉ ጠቁመው፥ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
መንገዱን ለማስተካከል የትራፊክ ፖሊሶችና ባለድርሻ አካላት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ ለመንገዱ ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጠው ችግሩ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሳምሶን ተስፋዬ ከወልዲያ ደሴና ከደሴ ወልዲያ በሚወስደው መንገድ ውጫሌ ከተማ መግቢያ የሚገኘው ድልድይ በአሸባሪው ህወሓት መሰበሩን አስታውሰዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የተሰበረው ድልድይ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፥ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዛሬ በመንገድ ብልሽት የተከሰተውን የመንገድ መዘጋት በፍጥነት በመፍታት ለተሽከትካሪ እንቅስቃሴ ክፍት እንደሚደረግም ነው የገለጹት።
በይከበር አለሙ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!