በክፍለ ከተማው ብቻ ባለፉት 6 ወራት ከ48 ሺህ ካሬ በላይ በህግ ወጥ መንገድ የተወረረ መሬት ማስመለስ ተችሏል
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ48 ሺህ ካሬ በላይ በህግ ወጥ መንገድ የተወረረ መሬት ማስመለሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሻምበል ኑርልኝ ገብረኪዳን እንደገለጹት÷ በክፍለ ከተማው በሕገ ወጥ መንገድ የተወረሩ 25 ቦታዎች በጥናት ተለይተው 22ቱን ለመሬት ባንክ ማስመለስ ተችሏል፡፡
ቀሪ ሶስት ቦታዎች በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ በመሆናቸው እየተጣራ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው÷በአጠቃላይ 48 ሺህ ካሬ መሬት ማስመለስ መቻሉን በመስክ ምልከታ ማረጋገጥ መቻሉንም ሃላፊው ገልጸዋል ።
በክፍለ ከተማው የሚገኙት የደንብ ማስከበር ኦፊሰር አደረጃጀት በክፍለ ከተማው የሚካሄዱ ሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ሁነቶች በሠላም እንዲጠናቀቁ ከሌሎች አጋራ የጸጥታ ተቋማት ጋር በርካታ ሥራዎችን መስራት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች አካባቢያቸውን በመጠበቅ ለጥፋት ተግባር ሊውሉ የነበሩ ጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋልን ጨምሮ በርካታ ተመሣሣይ የፀጥታ ስጋቶችን ማክሸፍ መቻሉን ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የደንብ መተላለፍ ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እዮብ ከበደ በበኩላቸው ÷ ደንብ ማስከበር በአሁኑ ወቅት የመፍትሔ አካል ሆኖ በከተማችን በርካታ የሰላም እን ጸጥታ እንዲሁም ሕገ ወጥ ተግባራትን የመከላከል ሥራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከመልካም አስተዳደር ችግርና ብልሹ አሰራር ጋር በተገናኘ አራት የወረዳ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን እና በተዋረድም በ59 የበታች ፈጻሚ ሰራተኞችና ባለሙያዎች ላይ በጥፋታቸው ልክ ማስረጃ በማደራጀት አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!