Fana: At a Speed of Life!

በጦርነት የተጎዱ ት/ቤቶችን መልሶ ለማደራጀት እና የአገሪቱን ት/ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች የወደሙ እና የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም በአገሪቱ የትምህር ቤቶቹን ስታንዳርድ ለማስጠበቅ ከ100 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚጠይቅ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
 
ሚኒስቴሩ የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት አቅርቧል፡፡
 
ሪፖርቱን ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርህኑ ነጋ÷ በአገሪቱ የነበረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አንስተዋል፡፡
 
ዘርፉ በራሱ ሰፊ እና ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ችግሮቹ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈቱ አይደሉም ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፡፡
 
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ÷በአገሪቱ 1 ሺህ 200 ትምህርት ቤቶች በጦርነት እና በሌሎች ግጭቶች ሲውድሙ÷ ከ5 ሺህ በላይ ትምህር ቤቶች ደግሞ ተዘግተዋል፡፡
 
በዚህ ምክንያትም 3 ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ÷ ከ150 ሺህ በላይ መምህራንም ከመማር ማስተማር ስራ ውጪ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
 
በተመሳሳይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል 3 ዩኒቨርሲቲዎች በከፊል እና በሙሉ መውደማቸው ነው የተገለጸው፡፡
 
በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች እና ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርገው የተመለሱ 22 ሺህ ተማሪዎች እና 1 ሺህ 500 መምህራን ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዛወሩ መደረጉንም አውስተዋል፡፡
 
6 ሺህ 200 ተማሪች ደግሞ በምዝገባ ሂደት መረጃ ባለማሟላት እና ምዝገባውን ባለማከናወናቸው ምክንያት ማዛዋወር አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡
 
በሪፖርቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ከ130 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማሰባሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
 
በሀይለየሱስ ስዩም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.