መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት የተቀናጀ ዘመቻ ሸኔ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ሁለት ማሰልጠኛዎች ወደሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)ከአሸባሪው ህወሃት ጋር እየተናበበ የሴራ ድሩን የዘረጋው ሸኔ ፣ የጥፋት ቡድን አባላቱን ያሰለጥንባቸው የነበሩ ሁለት ማሰልጠኛዎቹ መደምሰሳቸውን የምስራቅ ዕዝ አንድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብ/ጀ አዲሱ መሐመድ እና በፌዴራል ፖሊስ የምስራቅ ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን 5 አዛዥ ከማንደር አህመድ ፈዮ ገለጹ።
አዛዦቹ ሰንቀሌና ቀልቀልቲ የተሰኙት ማሰልጠኛዎችን ማውደም የተቻለው የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት ከዲቪዥኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጋር በትብብር ባደረጉት የተቀናጀ ዘመቻ ነው ብለዋል።
በማሰልጠኛው ውስጥ በስልጠና ላይ የነበሩትን ጨምሮ ተተኳሾችና የጦር መሳሪያዎች መማረካቸውንም አመራሮቹ ገልፀዋል።
የአሸባሪው ህወሓትን ተልዕኮ ለማስፈፀም እየሰሩ ያሉት የሸኔ አባላት ላይ የሚደረገው ምንጠራ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የገለፁት የክፍለጦሩ ዋና አዛዥ እና የፌዴራል ፖሊስ የምስራቅ ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን 5 አዛዥ ፣ በቅርቡ በተደረገ ዘመቻ ከ100 በላይ የአሸባሪው ሸኔ አባላት መደምሰሳቸውንና ከ600 በላይ ደግሞ መማረካቸውን ተናግረዋል።
ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በየአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ባደረጋቸው ጥቆማዎችና ትብብር መሆኑን አውስተው ፣ ቀጣይም ህብረተሰቡ የኢትዮጵያን ጠላቶች አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው ፣ የመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ሀገርን ከብተና ለማዳን በከፈሉት መስዋዕትነት ለተገኘው ሰላም ምስጋና ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ በተደረገው ዘመቻ የሚሊሻ አባላትን በማሰለፍ ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለውን ሎጀስቲክሳዊ አቅርቦት ለመከላከያ ሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን ያወሱት ዋና አስተዳዳሪው ፣ ሸኔን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።