ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍና አህጉራዊ ሁነቶችን በስኬት ማጠናቀቋ ሁለንተናዊ ድል ነው – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍና አህጉራዊ ሁነቶችን በስኬት ማጠናቀቅ መቻሏ የዲፕሎማሲያዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ፥ በድምርም ሁለንተናዊ ድል መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ መሀመድ ሰዒድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የተካሄዱት ሁነቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላትን ተደማጭነት እንደሚጨምሩ ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሲሰራጩ የከረሙትን ሀሰተኛ መረጃዎች ከማጋለጥ ባሻገር የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት መዋዕለ ንዋያቸውን በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲያፈሱ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ገበያ ማህበር ፕሬዚዳንት ጌታሁን ዓለሙ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ የተዘጋጁ ትና በስኬት የተጠናቀቁት ሁነቶች ለ የተዛባና ሀሰተኛ መረጃ ሲፈበርኩ የቆዩትን ኃይላት በማሳፈር የሀገራችንን እውነተኛ ገጽታ ማሳየት የቻሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች የተሰራጩትን የሀሰት ዘገባዎች በማምከን የኢትዮጵያን ገፅታ ከመገንባት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ሁነቶችን ተከትሎም በኮቪድ -9 እና በፀጥታ ችግር ተቀዛቅዞ የቆየው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ማሳየቱን ለአብነት ያነሳሉ፡፡
ይህም ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ትክክለኛ ገጽታ ያገናዘበ ወቅታዊ መልዕክት ያስተላልፋል ነው ያሉት፡፡
የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፥ ጨዋነትና ተባባሪነት የሚመሰገን መሆኑን ያወሱት ምሁራኑ÷ ይህ እሴት ተጨማሪ ሃብት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
በሀገራችን የሚስተናገዱ መሰል ሁነቶች ተጨማሪ ሲሳይ ይዘው እንዲመጡ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም በዋነኛነት መንግስት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ