በጋምቤላ ቦንጋ ፖሊስ ማሠልጠኛ ማዕከል ሠልጣኞች የጤና እክል ገጥሟቸዉ እንደነበር ተገለፀ
አዲስ አበባ፣የካቲት 1፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በጋምቤላ ክልል በቦንጋ ፖሊስ ማሠልጠኛ ማዕከል ሠልጣኞች የሆኑ 130 የሚጠጉ የልዩ ኃይል አባላት የጤና እክል ገጥሟቸው እንደነበር የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ÷ ሠሰልጣኞቹ የገጠማቸው የጤና እክል መነሻው ምን እንደሆነ በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሠልጣኞቹ ከተመገቡት ምግብና ከመጠጣቸው ናሙና ተወስዶ ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ መላኩንና ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
ኅብረተሰቡ ከአላስፈላጊ አሉባልታ ወሬዎች ራሱን በማራቅ ውጤቱን በትዕግሥት እንዲጠብቅም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሩ ÷ ሠልጣኞቹ ትላንት ምሽት ከ1:30 ጀምሮ ወደ ሆስፒታሉ ሄደው ተገቢው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ከታካሚዎቹ መካከል ለሕይወት የሚያሰጋ የጤና እክል የደረሰባቸው እንደሌሉ ገልፀው አብዛኞቹ አገግመው ወደ ማሠልጠኛ ማዕከላቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል።
ወደ ጋምቤላ የመጀመሪያ እና አጠቃላይ ሆስፒታል የሄዱት ሠልጣኞች ወደ 130 የሚጠጉ ሲሆን ከሠልጣኞቹ መካከል ሕክምና አግኝተው አብዛኞቹ ወደ ሥልጠና ማዕከሉ የተመለሱና ሕክምና በመከታተል ላይ ያሉም እንደሚገኙበት ከጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬተሪያት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።