Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በአሻባሪው ሸኔ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች በሽብርተኛው ሸኔ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
 
ነዋሪዎቹ ከፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
 
ነዋሪዎቹ የኦነግ ሸኔ አባላት በወረዳው በተለያዩ ቦታዎች የህዝብ መገልገያዎችን በማውደም እና በመዝረፍ እንዲሁም በማቃጠል ነዋሪዎችን በመግደል፣ በማገት፣ ሴቶች እና እናቶችን ደግሞ በመድፈር እና በማስደፈር ከፍተኛ ሰብዓዊ ጥሰት ሲፈፅም መቆየቱን ጠቁመዋል።
 
ቡድኑ በዞኑ በሚገኙ የህዝብ መገልገያዎች እና መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት በማድረስ ህዝቡ አገልግሎት እንዲነፈግ አድርጓል ነው ያሉት።
 
አሁንም የሽብር ቡድኑ በዞኑ በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቀዋል፡፡
 
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፈለው አደሬ ÷በዞኑ ባለፉት9 ወራት ውስጥ ብቻ በአሸባሪው ሸኔ ምክንያት ከ195 በላይ ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር አቁመው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
 
የሽብር ቡድኑ 88 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደግሞ ሙሉ በሙሉ እንዲወድሙ በማድረግ በአጠቃላይ ከ65 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዲወጡ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
 
ከዚህ ባለፈም በርካታ የጤና ተቋማት በሽብር ቡድኑ በመውደማቸው ከ435 ሺህ በላይ ዜጎች የጤና አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን አንስተዋል።
 
በአሁኑ ሰዓት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ የፀጥታ ማዋቅሩ በቅንጅት በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷የሸኔ የሽብር ቡድን ህብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ለቡድኑ ሲላላኩ የነበሩ ወጣቶችም በመንግስት ጥሪ ወደህብረተሰቡ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል።

 በሌላ በኩል በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሲያደርስ የነበሩ ከ500 በላይ የሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት፡፡
 
በምንይችል አዘዘው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.