ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ እና ብልጽግናን ከማምጣት የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ሕልም ጋር በቀጥታ የተቆራኘ አንኳር ጉዳይ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ አርዓያ ያደረገ እና የምትታወቅበት መገለጫ ሆኗል፡፡
መርሐ ግብሩ የተመጣጠነ ዝናብ እንዲኖር፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር እና በምግብ ራስን ለመቻል ትልቅ እገዛ እያደረገም ይገኛል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባራት እንደ ሀገር በተጨባጭ የደን መመናመንን በማስቀረት ሽፋኑን ማሳደግ ተችሏል፡፡
ለካርበን ሽያጭና ዛፍ መትከል ስለሚያስገኘው የቢሊየን ዶላሮች የኢኮኖሚ ምንጭ ማወቅ የአሁኑ ዘመን የሕልውና እና የብልጽግና መሠረትን ለመረዳት ወሳኝ መነሻ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከመቋቋም ባለፈ ታላቅ ሀገራዊና አሕጉራዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን÷ ይህ ታሪካዊ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በማሳደግ አዲስ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ጊዜያዊ ዘመቻ ሳይሆን የሀገርን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውና የምግብ ዋስትናን በተግባር የሚያረጋግጡ የፍራፍሬ ዝርያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች በመተከላቸው የአርሶ አደሩን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየሩ ይገኛሉ።
ከተከላው ጎን ለጎን ችግኞችን በማፍላትና በመንከባከብ ሂደት ውስጥ ለሚሊየኖች ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከሉ ችግኞች ከከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው በካይ ጋዝ የመምጠጥ እና የማከማቸት አቅም ስላላቸው ለኢትዮጵያ አዲስ እና ዘላቂ የዶላር መገኛ መስመር እየከፈቱም ይገኛሉ።
መርሐ ግብሩ ከሀገራዊ ፋይዳው ባሻገር የኢትዮጵያን ስልታዊ የውጭ ፖሊሲ እና ቀጣናዊ ትስስር የሚያጠናክር የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ መሳሪያ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ለጂቡቲ፣ ለኬንያ፣ ለሶማሊያ እና ለደቡብ ሱዳን በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በነጻ በማካፈል በጋራ የመልማትና ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሀብትን በጋራ የመጠበቅ ራዕይን በተግባር አሳይታለች።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዛፍ ከመትከል በእጅጉ የላቀ፣ ሀገራዊ ብልጽግናን ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ጋር ያስተሳሰረ ታላቅ ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው። ይህ ንቅናቄ ለተተኪው ትውልድ የሚለምልም እና የሚጠቅም ሕያው ቅርስ እና የማያረጅ ውርስ ጥሎ የሚያልፍ የአዲሱ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ማሳያ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄው ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት እያደረገም ይገኛል።
በወንድማገኝ ጸጋዬ