በአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ይሳተፋሉ አለ የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት÷ የወጣቱን ሰብዕና በመገንባት በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል ለማድረግና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላለፉት አራት ዓመታት በተከታታይ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰው፥ ዘንድሮም ለ5ኛ ጊዜ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቅቋል ነው ያሉት።
በ2018 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሳተፉ 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች 5 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
በአገልግሎቱ 15 ሚሊየን የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለጹት ኃላፊዋ፥ 20 ቢሊየን ብር የሚገመት የመንግሥት ወጪ ለማዳን እቅድ ተይዟል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው 17 የሥራ ስምሪቶችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፥ 18 ሺህ 854 ቤቶችን በማደስ እንዲሁም 9 ሺህ 432 አዳዲስ ቤቶችን ገንብቶ ለማስረከብ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ማደስና አዲስ መገንባት፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረስ፣ የግብርና፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እና የትምህርት መሣሪያዎችን ለተማሪዎች ማሟላት የመሳሰሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ይሰጣሉ ብለዋል፡፡
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሐምሌ 1 ቀን 2018 እስከ መስከረም 20 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን፤ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።
በደሳለኝ ቢራራ