Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ሠላምና ብልጽግና በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከክልላዊ አስተዳደሮች ብሎም ከማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሀገሪቷ ሠላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ቀጣይ ጉብኝት የምዕራፍ ጅማሮ በኦሮሚያ ክልል አዳማ በአሜሪካ መንግስት የተሠሩ መሰረተ-ልማቶችን ጎብኝተዋል፡፡

አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ከአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ጋር በመሆን ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውም ነው የተነገረው ፡፡

አምባሳደር ጃኮብሰን፥ በአሜሪካ በጤናው ዘርፍ የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን፥ ወጣቶችንም አግኝተው ማወያየታቸው ነው የተመለከተው፡፡

ቀጣይ በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ ጋር መምከራቸውም ነው የተጠቆመው።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ፥ በኦሮሚያ በተለይም በአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ ከፍ ሲልም በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች እና ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር የሚችሉ ዕድሎች ላይ ከአምባሳደሯ ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል።

በመቀጠልም በአሜሪካው የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል የ3 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል የተገነባውን በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ክልላዊ ላቦራቶሪ መጎብኘታቸው ታውቋል፡፡

አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን በክልሉ በሚገኘው በዚህ ላቦራቶሪ በበሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከላት ውስጥ የሚሰራውን የሕክምና ቡድን ማግኘታቸውም ነው የተነገረው፡፡

የሕክምና ቡድኑ በምሥራቅ ኦሮሚያ ዘጠኝ ዞኖች ነዋሪ የሆኑ ከ20 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በ58 ሆስፒታሎች እና 700 ጤና ጣቢያዎች እያገለገለ መሆኑም ነው የተመለከተው፡፡

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ያስችለው ዘንድም በክልሉ የሚገኙ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን በመጠነ ሰፊ ጉዳዮች ላይ በማወያየት ሥራ መጀመሩንም ነው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ ያመላከተው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.