የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያጋጠመውን ፈተና በመቀልበስ ወደ ሰላምና ልማት ለመመለስ የተሠራው ሥራ ውጤታማ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነበረበትን ፈተና በመቀልበስ ወደነበረበት ሰላምና ልማት ለመመለስ በበጀት ዓመቱ የተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊሀሰን ገለጹ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የ5ኛ ዓመት 8ኛ የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻሊ ሀሰን የክልሉን የ2014 የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በሪፖርቱ እንደተገለጸው÷ የአርሶ አደሩን ልፋት በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሜካናይዝድ እርሻ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በተሰራጩት 34 ትራክተሮች ከ11 ሺህ 400 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም ከቆላማና መስኖ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተገዙ 60 ትራክተሮች ወደ ክልሉ እየተጓጓዙ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተጠናቀቀው የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 341 ሺህ 197 ሄክታር መሬት 14 ሚሊዮን 447 ሺህ 272 ኩንታል ምርት መገኘቱም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
የክልሉን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለማልማት በተሰጠው ትኩረት÷ ዘርፉ ከክልሉ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ ማበርከት መጀመሩን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በበጀት ዓመቱ 13 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 375 ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሠማሩ ፈቃድ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከልዩ አነስተኛ እና ከባህላዊ ወርቅ አምራች ማኅበራት 23 ኩንታል ወርቅ ወደብሔራዊ ባንክ እንዲገባ መደረጉንም ነው ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት ሪፖርት ያመላከተው፡፡
እንዲሁም በ2014 ዓ.ም 301 ሺህ 780 ቶን የድንጋይ ከሠል እና 725 ቶን የእብነበረድ ምርት ተገኝቷል ነው የተባለው፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ማዕድናት ፈቃድ ማውጫ፣ ከሮያሊቲ፣ ከመሬት ኪራይና ፈቃድ ዕድሳት 48 ሚሊየን 951 ሺህ 488 ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነበረበትን ፈተና በመቀልበስ ወደነበረበት ሰላምና ልማት ለመመለስ በበጀት ዓመቱ የተሠራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አቶ አሻድሊሀሰን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
የህወሓት ተላላኪ ኃይሎች በመተከልና ካማሺ ዞኖች በንጹሃን ላይ ሲያደርሱት የነበረውን ጥቃት ጠቁመው÷ የክልሉ መንግስት ፈተናውን በመቀልበስ የዜጎችን ህይወት ለመታደግና ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸው ሥራዎች የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡
በመተከል ዞን በ108 ቀበሌዎች 63 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የእርቀ ሰላም ጉባዔዎች መካሄዳቸውን የገለጸው ሪፖርቱ÷ በዚህም 82 ሺህ 825 የተፈናቀሉና በጫካ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደቀያቸው መመለሳቸውን አመላክቷል፡፡
በክልሉ በተከናወነው ሕግ የማስከበር ሥራ÷ 157 ፀረ- ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን እና 791 ያህሉ ደግሞ መማረካቸውን እንዲሁም በፀረ- ሰላም ኃይሎች ታፍነው የነበሩ 99 ወገኖችን ማስለቀቅ መቻሉን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ወጣቶችን እየመለመሉ ወደጥፋት ሲያስገቡ የነበሩ 42 መልማዮችና ከ47 ግብረ አበሮቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ለሕግ መቅረባቸው ተገልጿል፡፡
ጉባዔው የክልሉ የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም፣ የ2014 በጀት ዓመት የጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የዋና ኦዲት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የ2014 ተጨማሪ የበጀት አዋጅ፣ የክልሉ የ2015 ረቂቅ በጀት መርምሮ ማጽደቅ፣ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሚዲያን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባዔው በሁለት ቀን ቆይታው÷ በ12 አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡