Fana: At a Speed of Life!

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 843 ተማሪዎች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 843 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው በዚህ ወቅት ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሰለጠናችሁበት መስክ ስራ በመፍጠርና ችግር ለመፍታት አደራ የምትቀበሉበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም በተማራችሁበት መስክ ለሀገርና ለትውልድ ፋይዳ ያለው ስራ በመስራት አደራችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ተመራቂዎች የሀገር ተስፋ እና የለውጥ አርማዎች ናችሁ ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ናቸው፡፡

ታማኝነት፣ ተጠያቂነትና ትጋት መለያችሁ ሊሆን ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ወደ ስራ ዓለም ስትገቡም ማህበረሰብን አክባሪ፣ አገልጋይነትን የተላበሰና ሀገርን የሚያሻግር ትውልድ መሆን ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከ56 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።

በሰብለ አክሊሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.