ኮሚቴው ሰብአዊ እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የሚደረግን ያልተፈቀደ ጥሬ ገንዘብ እና እቃዎች ዝውውር አወገዘ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሰብአዊ እርዳታ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ውስጥ የሚደረግን ያልተፈቀደ ጥሬ ገንዘብ እና ሌሎች እቃዎች ዝውውርን በፅኑ አወገዘ።
ኮሚቴው በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው በአፋር ክልል በሰርዶ ኬላ በኪራይ የመጣ መኪና አሽከርካሪ ገንዘብ እና ሌሎች ያልተፈቀዱ ዕቃዎችን ሲያጓጉዝ መገኘቱን አስታውሷል።
ተሽከርካሪው ሰብአዊ እርዳታ የጫነ እና በጣም አስፈላጊ የሆኑ የህክምና እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ ክልል በማጓጓዝ ላይ የነበረ መሆኑንም አስታውቋል።
ያልተፈቀደው ገንዘብ እና እቃው በመደበኛው አሰራር ሰብአዊ እርዳታ በጫነው ተሽከርካሪ ላይ በተደረገ ፍተሻ በባለስልጣናት የተገኘ ሲሆን በኪራይ የመጣው መኪና አሽከርካሪም በቁጥጥር ስር ውሏል ነው ያለው።
በኪራይ የመጣው የንግድ መኪና አሽከርካሪም ሰብአዊ እርዳታውን በጣም ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማጓጓዝ ላይ ብቻ ትኩረት መስጠት ሲገባው ይህን አለማድረጉንም ነው ኮሚቴው ያስታወቀው።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ከዚህ ያልተፈቀደ ገንዘብ እና እቃዎች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን በመጥቀስም ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚያወግዝም ገልጿል።
ኮሚቴው በመላው ኢትዮጵያ በግጭት እና በሌሎች ምክንያቶች የተጎዱ ሰዎችን ለመከላከል እና ለመርዳት ብቻ የሚፈልግ የሰብአዊ ድርጅት መሆኑን በመግለጽም፥ የተፈጠረው ኹነት ኮሚቴው በሚያከናውነው ሰብአዊ ተግባር እና አስፈላጊ የእርዳታ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር እየሰራሁ ነው ብሏል።
ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሙሉ በሙሉ በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!