ህወሓት የጀመረውን ጦርነት አቁሞ ወደ ሠላም ንግግር እንዲመጣ የትግራይ ህዝብ ጫና እንዲፈጥር የመከላከያ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ህዝብና የትግራይ ወዳጆች ህወሓት የጀመረውን ጦርነት በአስቸኳይ አቁሞ ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጣ ጫና እንዲፈጥሩ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ሚኒስትሩ ÷ በትግራይ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ምሁራን ፣ ዳያስፖራዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ስለ ሠላም እንዲዘምሩና ህወሓት ጦርነት አቁሞ ወደ ሠላማዊ ውይይት እንዲመጣ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የትግራዋይ እና የትግራይ ጉዳይ በዘላቂነትና ህዝብን በሚጠቅም መልኩ ዕልባት ማግኘት የሚችለውም በውይይትና በሠላማዊ መንገድ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የሀገሩ ተሥፋና የህዝቡ መሪ መሆን የሚችለው ወጣቱ ትውልድ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ኪሳራ ያጋጠማቸውን ዕድሜያቸውን የጨረሱ ግለሰቦች መንበረ-ሥልጣን ለማራዘም ሲባል ወደ ተከታታይና ትርጉም የለሽ ጦርነት መማገድ እና ሕይወቱ መቀጠፍ የለበትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ትግራዋይና የትግራይ ተቆርቋሪ፣ ህወሓት የሚሰጣቸውን አጀንዳ ወደጎን በመተው፣ አጀንዳቸውን ህዝብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡