Fana: At a Speed of Life!

ወልዲያ ወደቀደመ እንቅስቃሴዋ መመለሷ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐሰተኛ መረጃና በአሉባልታ የተወሰነ አለመረጋጋት ታይቶባት የነበረችው ወልዲያ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷ ተገለጸ፡፡

ወልዲያ ከተማ ከሰሞኑ በወራሪው ህወሓት ስምሪት ተሰጥቷቸው ወደከተማዋ የገቡ ሰርጎ ገቦች ከተማዋ በአሸባሪው ቡድን ልትያዝ መሆኑን በነዙት የማደናገሪያ አሉባልታ ጥቂት የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሄዳቸው ይታወሳል፡፡

ሆኖም ማህበረሰቡ አሸባሪው አሉባልታ እያራገበ መሆኑንና የጥምር ጦሩ ውጤታማ የመከላከልና የማጥቃት እንቅስቃሴ መሆኑን ሲረዱ ወደአካባቢያቸው መመለሳቸው ነው የተገለጸው፡፡

አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ግን አሉባልታውን ወደጎን ብሎ ሰራዊቱን እያበረታታና ስንቅ እያቀበለ መሰንበቱን ማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ወልዲያ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ ሆቴሎች፣ ሱቆችና የመንገድ ዳር አገልግሎቶችና መደበኛ እንቅስቃሴዋን ጀምራለች፡፡

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ካሳ ፥ አጠቃላይ የጸጥታ መዋቅሩ የከተማዋን በሮች የማስጠበቅ ስራ እየሰራ መሆኑንና በጸጥታውም ይሁን በግብዓት አቅርቦት የነዋሪው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የወልዲያ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዳዊት መለሰ ፥ ህብረተሰቡ የተለመደውን የህወሓት ማደናገሪያ በመስማት እንዳረበሽና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከሰጡት ማረጋገጫ ውጪ በሌሎች ማደናገሪያዎች ሳይረበሽ ከመንግስት ጎን ሆኖ ከተማውን ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የሰርጎ ገቦችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሰዓት እላፊን ጨምሮ ሌሎችም የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ሰርጎ ገቦችን የማጥራትና በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉም ተነስቷል፡፡

ነዋሪው የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተመልክቷል፡፡

በአንድነት ናሁሰናይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.