ኢትዮጵያ፣ ከተረጂነት ወደ ሉዓላዊነት…
የኢትዮጵያ ከተረጂነት ወጥቶ ወደ ወጪ ምርት ላኪነት መሸጋገር የታሪካዊ ጉዞ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ አስርት ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረክ ከምግብ ዋስትና እጥረት እና ከዕርዳታ ጥገኝነት ጋር ስሟ ተያይዞ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በመደመር እሳቤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱ ይህንን የተረጂነት ታሪክ በመቀየር ወደ አምራችነት እና ላኪነት ለመሸጋገር እያደረገችው ያለው ስትራቴጂካዊ ጉዞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።
ይህ ሽግግር የፖሊሲ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የሀገርን ክብር እና የኢኮኖሚ ነፃነት የማስከበር ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።
ይህ ታሪካዊ ሽግግር የተቀረፀው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ስር ነው። መንግሥት የውጭ ዕርዳታን እና ብድርን ከመጠበቅ ይልቅ የሀገር ውስጥ አቅምን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጓል። በተለይም ግብርናን ማዘመን፣ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት እና አርሶ አደሩን በቴክኖሎጂ መደገፍ የሽግግሩ ዋና መነሻዎች ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ላኪነት መሸጋገር ትልቁ ማረጋገጫ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ነው።
ቀደም ሲል በዓመት አንድ ጊዜ በክረምት ዝናብ ብቻ ይመረት የነበረውን ስንዴ፣ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በበጋ ወቅት በመስኖ ማምረት ተጀምሯል።
ሀገሪቱ ለስንዴ ግዢ ታወጣ የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል።
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ፍጆታን አሟልታ ትርፍ ምርትን ለጎረቤት ሀገራት እና ለዓለም አቀፍ ገበያ መላክ ጀምራለች።
ሌላው የሽግግሩ ምሰሶ የሆነው የሌማት ትርፋት ብሔራዊ ንቅናቄ ነው። ይህ መርሃ-ግብር ትኩረቱን በዶሮ እርባታ፣ በወተት ምርት፣ በንብ ማነብ እና በስጋ ልማት ላይ አድርጓል።
እያንዳንዱ የገጠርና የከተማ ነዋሪ በጓሮው የአመጋገብ ሥርዓቱን እንዲያሻሽል እና የተረፈውን ምርት ለገበያ በማቅረብ ገቢ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡
ይህ ንቅናቄ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ማህበረሰቡ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ አኗኗር ወጥቶ ወደ ንግድ ስራ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር፣ የኢንዱስትሪ እና የንግድ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢትዮጵያ የውጭ የንግድ ዘርፏን ለማሳደግ እና የምርት አይነቶችን ለማብዛት ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡
ቡና፣ ቅባት እህሎች እና የቆዳ ውጤቶችን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ተጨምሮባቸው እንዲላኩ መደረጉ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን አሳድጎታል።
የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ነፃ ማድረግን ጨምሮ በቅርቡ የተወሰዱ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች ላኪዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ላኪነት የመሸጋገር ጉዞ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የሀገርን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውሳኔ ሰጪነት ነፃነት የሚያረጋግጥ ታላቅ እርምጃ ነው።
ይህ ሥራ ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የምግብ ጎተራ የመሆን ራዕይዋን በቅርብ ዓመታት ውስጥ እውን እንደምታደርግ ጥርጥር የለውም።