የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት የመደመር እሳቤን በተግባር …
የመደመር እሳቤ የሀገር በቀል እውቀትንና አቅምን ማዕከል በማድረግ፣ ትላንትንና ዛሬን አቀናጅቶ የተሻለችና የበለጸገች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ታላቅ ራዕይ ነው።
ይህ እሳቤ በንድፈ-ሐሳብ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን፣ በተግባር መሬት ወርዶ የህዝብን ህይወት መቀየር እንደሚችል ማረጋገጫ ከሆኑት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ ነው።
ቀደም ሲል ለብክለት፣ ለቆሻሻ መጣያነትና ለደህንነት ስጋት የነበረው የ10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት የወንዝ መስመር ወደ ውብ የስነ-ምህዳር መናፈሻነት የተቀየረ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የመደመርን ዋና ዋና ምሰሶዎች በተግባር አሳይቷል፡፡
የመደመር እሳቤ አንዱ መርህ፣ የነበሩ ህጸጾችን ማረምና ማሻሻል ነው።
ለአመታት የአዲስ አበባ ወንዞች የፋብሪካና የቤት ውስጥ ቆሻሻ መፍሰሻዎች ነበሩ።
የእንጦጦ-ቀበና ፕሮጀክት ግን ይህንን የዘመናት የታሪክ ጠባሳ በመቀየር፣ ወንዙን የከተማዋ አዲስ ሳንባ አድርጎታል።
87.6 ሄክታር መሬትን አረንጓዴ በማልበስ እና ከ50 ሺህ በላይ ውብ ዛፎችን በመትከል፣ የከተማዋን የስነ-ምህዳር ሚዛን መመለስ ተችሏል።
በሌላ በኩል ይህ ፕሮጀክት የተገነባው ሙሉ በሙሉ በሀገር በቀል መሐንዲሶች፣ ወጣቶችና ባለሙያዎች አቅም ነው።
ቀደም ሲል ለትላልቅ ግንባታዎች የውጭ ድጋፍና እውቀትን ብቻ የመጠበቅ ልምምድን በመስበር፣ የኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስን በተግባር ሀገር በቀል አቅምን በማቀናጀት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማሳየት ተችሏል።
ፕሮጀክቱ የወጣቶችን ጉልበት፣ የመሐንዲሶችን እውቀትና የመንግስትን ቁርጠኝነት በማቀናጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል።
የመደመር እሳቤ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ አለበት ብሎ ያምናል፡፡
እነዚህም ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ናቸው። ይህ ፕሮጀክትም ይህንን መርህ ፈትኖ በተግባር አረጋግጧል፡፡
ለነዋሪዎች ነጻ የዕረፍት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የልጆች መጫወቻ እና የ33.2 ኪሎ ሜትር መንገድ የእግር ጉዞ ስፍራዎችን በመፍጠር የዜጎችን የአእምሮና የአካል ጤንነት ያድሳል። ይህ ማህበራዊ ፋይዳው ነው፡፡
በወንዙ ዳርቻ የተገነቡት ሱቆችና ካፌዎች ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በተጨማሪም አዲስ አበባን በአፍሪካ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።
በፕሮጀክቱ ውስጥ የተገነቡት የተንጠልጣይ ድልድዮችን ጨምሮ 21 ዘመናዊ የእግረኛ ድልድዮች የከተማዋን ክፍሎች ማገናኘት ብቻ ሳይሆን፣ በወንዙ ግራና ቀኝ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን በማህበራዊ ህይወት የሚያስተሳስሩ የሰላምና የአብሮነት ተምሳሌቶች ናቸው።
ፕሮጀክቱ ድሃና ሀብታም ሳይለይ እኩል የሚዝናናበት የህዝብ መድረክ ሆኗል።
የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ መደመር በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ መሆኑን የመሰከረ ታላቅ የትውልድ አሻራ ነው።
ትላንት ይሸትና ያስፈራ የነበረውን ስፍራ ዛሬ መልካም ጠረን የሚሸተትበትና ነዋሪው የሚኮራበት ውብ ስፍራ በማድረግ፣ የኢትዮጵያን አዲስ የከፍታ ጉዞ በግልጽ ያሳያል።