ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ሬዳዋ ሞተርስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት ተፈራሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት ተፈራረሙ።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው÷ ፓርኩ በድሬዳዋ ከተማ የሚገነባ ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ የሚገነባው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅም 23 ኢንዱስትሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ቴሬሳ እንደገለጹት÷ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ነች፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር የግል ባለሀብቱ ሚና ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ “ለዚህ ዓላማ መሳካት ደግሞ የምንሳሳው ጉልበት እና የምንቆጥበው ሀብት የለም” ነው ያሉት፡፡
ሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ ፓርክ በድሬዳዋ ከተማ በ116 ሔክታር ላይ በሀገር ውስጥ ባለሀብት የተገነባ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን÷ ለግንባታው 5 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
በበረከት ተካልኝ