በባሕርዳር ከተማ ከ391 ሚሊየን ብር በላይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ስምምነት ተፈጸመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕርዳር ከተማ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ከዓለም ባንክ በተገኘ የብድርና እርዳታ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ለመገንባት የውል ስምምነት ተፈጽሟል።
ውሉ የተፈጸመው በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የበላይነት በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት እና በስድስት ተቋራጮች መካከል ሲሆን፥ ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ 391ሚሊየን 856 ሺህ ብር ወጪ ይደረግበታል ነው የተባለው።
በተፈፀመው ስምምነት መሰረት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች 20 አዳዲስ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ 30 አዳዲስ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ 13 ነባር የሕዝብና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ጥገና እና 20 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፍሳሽ ማስወገጃ ናቸው።
የባሕዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባየ አለባቸው በከተማዋ የውኃ ፍሳሽ እና ንፁሕ መፀዳጃ ቤቶች ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ ፕሮጀክቶች ችግሮችን በመቅረፍ በኩል ድርሻቸው የጎላ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው በሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ባሕርዳር ፣ ጎንደር ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ከተሞች ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት።
አሁን ላይም የአማራ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በአራቱ ከተሞች ላይ ውኃና ፍሳሽ ላይ እየሠራ ነው ብለዋል።