በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን የሰደድ እሳት መቆጣጠር አለመቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2 ፣2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባለፈው መጋቢት 29 ቀን ጀምሮ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተከሰተውን የሰደድ እሳት እስካሁን መቆጣጠር አለመቻሉ ተገልጿል።
በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከ ቀኑ 9 ሰዓት ባልታወቀ ምክንያት መነሳቱ ተጠቁሟል።
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዛናው ከፍያለው እንደተናገሩት÷ እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ማህበረሰብ ቢሞክርም መቆጣጠር አለመቻሉንና ከ600 በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እሳቱን ለማጥፋት መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የቦታ አቀማመጡ ገደላማ መሆኑ እሳቱን ለመቆጣጠር ፈተና ሆኖብናል ያሉት ሃላፊው÷ እሳቱ ግጭ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በኩል እንደተነሳ አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ እስከ ዛሬ ማለትም እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ድረስ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በፓርኩ የተነሳውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡