ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየታየበት ነው- ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየታየበት ነው አሉ ተመካካሪዎች።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።
ጉባኤው በስልታዊ ቡድኖች ተደራጀተው የቀረቡ የምክክር ምክረ ሃሳቦች 500 አባላት ላሉት ለአጀንዳ የሥራ ቡድን ቀርበዋል።
ተመካካሪዎች ከሁለቱ ስልታዊ ቡድኖች ሃሳቦችን እንዲያቀናጁ 30 አባላት ያሉበትን የምክረ ሃሳብ አቀናጆችን የመረጡ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ቀናት የስልታዊ ቡድኖች ሃሳቦች በተመረጡ አቀናጆች ተዋህደው ይቀርባለው።
የጉባኤውን ሂደት አስመልክቶ ተመካካሪዎች እንዳሉት፤ ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባት እየታየበት ነው።
በተመካካሪዎች መካከልም አንዱ የሌላውን ሀሳብ የሚያዳምጥበትን ዕድል በመፍጠር፣ የጋራ መግባባትን የሚገነባና ተስፋን የሚያለመልም ሂደት መሆኑንም ተናግረዋል።
ጉባኤው ሁሉን አሳታፊና አካታች ስለሆነ የነበረውን አለመግባባትና ልዩነት በመፍታት ወደ አንድነት የሚያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያመጣና ተስፋን የሰነቀ ነው ብለዋል።
የምክክሩ ሂደት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሁሉም አካባቢ የመጡ ኢትዮጵያውያን የተሰባሰቡበት መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያመጣ እንደሆነም እምነታቸውን ገልጸዋል።