9 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ተሽከርካሪን ይዞ የተሰወረው ሹፌር በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልል ንብረት የሆነን 9 ሚሊየን ብር የሚያወጣ “ላንድ ክሮዘር ፕራዶ” ተሽከርካሪን ይዞ የተሰወረው ሹፌር በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።
የቅጣት ውሳኔው የተወሰነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የቅጣት ውሳኔ የተወሰነበት ተከሳሽ አሸናፊ ረዳኢ የሚባል ሲሆን÷በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ተከራይቶ ይኖር እንደነበር ጠቅሷል።
ተከሳሹ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ጽኅፈት ቤት ከመስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በሹፌርነት ተቀጥሮ ሲሰራ እንደነበር በክሱ ተገልጿል።
በዚህ ጊዜ ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ የሥራ ኃላፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥበት ተረክቦ የነበረውን ንብረትነቱ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሆነ የታርጋ ቁጥር ኮድ 4-01423 (ትግ) እንዲሁም የፕሮቶኮል ታርጋ ቁጥር ኮድ 2-76686 የሆነ ዘጠኝ ሚሊየን ብር የሚገመት ነጭ “ላንድ ክሮዘር ፕራዶ” ተሽከርካሪ በእጁ ይዞ መቆየቱ በክሱ ተመላክቷል።
ከሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ከነመኪናው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሽግግር መንግስት አስተዳደር ጽኅፈት ቤት ተዘዋውሮ እንዲሰራ የተመደበ ቢሆንም መኪናውን ይዞ የተሰወረና መኪናውን ያጠፋው መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቢህግ በከባድ የእምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።
ተከሳሹ በየካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የቀረበበትን ክስ ከደረሰውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል የዕምነት ክኅደት ቃሉን ሰጥቷል።
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ÷ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱልኝ አምስት ምስክሮች ስላሉኝ ይሰማልኝ ሲል ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም በተለያዩ ቀናቶች የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ቃል ካዳመጠ በኋላ ተከሳሹ የቀረበበትን የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።
ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃዎችን ያቀረበ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢ መንገድ ማስተባበል አልቻለም በማለት በተከሰሰበት የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበት ነበር።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶችን እና ዐቃቤ ሕግ ቅጣቱ ከፍ ብሎ እንዲጣልለት ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመያዝ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት ተከሳሹን በ6 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ አስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል።
በታሪክ አዱኛ