Fana: At a Speed of Life!

አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን በሱዳን የተፈጠረውን ችግር የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት መረጃ መሰረተ ቢስ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን በሱዳን ግጭት የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም÷ ኢትዮጵያና ሱዳን በመንግስታት መለዋወጥ ያልዋዥቀ ጽኑ ወዳጅ ጎረቤት ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
 
ሱዳን ካጋጠማት ወቅታዊ ፈተና እንድትወጣ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሁኔታ ከሱዳናዊያን ጎን መሆኗንም አረጋግጠዋል።
 
ያም ሆኖ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን በግጭቱ የኢትዮጵያ ጣልቃገብነት እንዳለ አስመስለው የሚያናፈሱት መረጃ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት የማይመጥንመሰረተ ቢስና ሀሰተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ይህን ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት በሱዳን የተፈጠረውን ችግር አካባቢያዊ ከማድረግ የመነጨ ፍላጎት መሆኑን ነው የገለጹት።
 
የኢትዮጵያ መሪዎች ከቀዳማዊ አጼ ኅይለሥላሴ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ ሱዳን ያጋጠሟትን ቸግርች በሰላም እንዲፈቱ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።
 
ዛሬም ሱዳን ላጋጠማት የሰላም መደፍረስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ የነበራትን ታሪካዊ ሚና ለመወጣት ሙሉ ፍላጎት እና ዝግጁነት እንዳላት አረጋግጠዋል።
 
ሱዳናዊያን ያለ ምንም የውጭ አካል ጣልቃገብነት ችግሮቻቸውን በራሳቸው ጥበብና ዕውቅት ይፈታሉ ብላ እንደምታምን ነው የተናገሩት።
 
ሚኒስቴሩ በሱዳን ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስን ተከትሎ በዋናው መስሪያ ቤት እና ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት በሀገሪቷ የሚገኙ ዜጎቻችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡
 
ለዚህም ከተለያዩ መስሪያ ቤቶችና አጎራባች ክልሎች በአባልነት ያቀፈ ግብረ-ኃይል በአገር አቀፍ ደረጃ መቋቋሙን ተናግረዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግጭት የገቡ የሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.