Fana: At a Speed of Life!

ፋይዳ ቨርስ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ጽኑ መሰረት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፋይዳ ቨርስ የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ጽኑ መሰረት ነው አሉ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሮ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር “ፋይዳ ቨርስ” በሚል ስያሜ ወደ ስራ መግባቱ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነውን “ፋይዳ ቨርስ ዲጂታል ሶሉሽንስ” ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ ተቋሙ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆኑ ቁልፍ ተግባራት አከናውኗል።

ተቋሙ 50 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎችን መመዝገቡንና ከ13 ሚሊየን በላይ የታተሙ ካርዶችን ማሰራጨት መቻሉን ጠቅሰው፥ ከ160 ሚሊየን በላይ የማረጋገጫ አገልግሎቶች መስጠቱን ተናግረዋል፡፡

በ13 ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የዲጂታል ማንነት መሠረተ ልማታችንን ማስተዋወቅ ችሏል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ተቋሙ “ፋይዳ ቨርስ” ተብሎ በድጋሚ እንዲቋቋም የተወሰነበትን ሂደት አብራርተዋል፡፡

ሽግግሩ ዲጂታል የሕዝብ መሰረተ ልማትንና ዲጂታል አስተዳደርን የሚያጠናክር እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትን የሚያሻሽል፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል ሥነ ምህዳርን ያጎለብታል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እሴት በመፍጠር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትሆን እንደሚያስችል ታምኖበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ፋይዳ ቨርስ የኢትዮጵያ ይፋዊ የዲጂታል መሰረተ ልማት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በፈረንጆቹ 2030 የኢትዮጵያን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት በ6 በመቶ እንዲያሳድግና 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲያመጣ ትልቅ እምነት ተጥሎበታል ነው ያሉት።

የዚህ ተቋም መመስረት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማዋል የገባችውን ቃል የምታድስበት ነው በማለት ተናግረዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.