የአውሮፓ ኅብረት ም/ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ የሚታይ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ በበጎ መልኩ እንደሚያየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ትብብር በአዲስ መልክ እንደገና ለማደስ አበክራ እየሠራች እንደምትገኝም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ካደረገው ስብስባ በኋላ ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ ምክር ቤቱ በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት ትግበራ ላይ የተገኙ ውጤቶችን ጨምሮ ለሌሎች ጉዳዮች ዕውቅና መሥጠቱን ገልጿል።
ኅብረቱ በዘላቂ ግብርናና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረውን ዓመታዊ የባለብዙ ዘርፍ የድጋፍ ፕሮግራም በድጋሚ ለመጀመር ያሳየው ዝግጁነት፣ አበዳሪ ሀገራት ባቋቋሙት የጋራ ማዕቀፍ ስር የሚከናወነው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የድርድር ሂደት በአፋጣኝ እንዲቋጭ ያቀረበው ጥሪና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማረጋጊያና ማሻሻያ አጀንዳ እንዲደግፉ የሰጠው ጠንካራ ማበረታቻ መልካም የሚባል እንደሆነም አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ አጋሮች ከሀገሪቷ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በአዲስ መልክ እያደሱ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ይህ እየሆነ ያለው ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥና ለማጽናት የተጀመረው ሂደት አበረታች ለውጦች በተመዘገቡበት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች፣ በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ማቋቋምና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ውጤቶች እየተገኙ ባሉበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!