ሀሰተኛ የወራሽነት ሰነዶችን በማቅረብ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሊቀበሉ ሲሉ ተይዘዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የወራሽነት ሰነዶችን በማቅረብ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ሊቀበሉ ሲሉ ተይዘዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ የአታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ መቶ አለቃ አዲስ አልቱ እና ሌተናል ኮሎኔል ሰለሞን አጥናፉ የሚባሉ ሲሆን÷ ክሱ የቀረበውም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
1ኛ ተከሳሽ ወራሽ ነኝ በሚል የማጭበርበሪያ ስልት በመጠቀም የግል ተበዳይ በሞት እንደተለዩ የሚገልጽ ሀሰተኛ የሞት የምስክር ወረቀት ማዘጋጀቱ በክሱ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በስሙ የተዘጋጀ ሀሰተኛ የፍርድቤት የወራሽነት ምስክር ወረቀት ማቅረቡ ነው በክሱ የተብራራው።
ባለቤትነቱ የግል ተበዳይ ወይዘሮ አልፍነሽ ኃይሉ የሆነ አቢሲኒያ ባንክ ቦሌ ኤርፖርት ቅርጫፍ የተከፈተ የቁጠባ ሒሳብ ውስጥ የሚገኝ 10 ሚሊየን 210 ሺህ 669 ብር ከ11 ሳንቲም ለመውሰድ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ ከተማ የባንኩ ሳሪስ ቅርጫፍ ሀሰተኛ የወራሽነት ሰነዶችን አዘጋጅተው በመጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ/ም ማቅረባቸው በክሱ ተዘርዝሯል።
ሁለተኛ ተከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ የወራሽነት ሰነዶችን በጋራ በመሆን ለባንክ ካቀረቡ በኋላ ትክክለኛ ሰነድ ነው በማለት በፍጥነት ጉዳዩ እንዲፈጸም እና ባንኩ የተሳሳተ እምነት አድሮበት ህገ ወጥ ክፍያ እንዲከፍል ጫና መፍጠሩ በክሱ ተካቷል።
ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ ገንዘቡን በሀሰተኛ የወራሽነት ማስረጃ አቅርበው ገንዘቡን ለመውሰድ ሲሉ መያዛቸውም ነው የተጠቀሰው።
በዚህም÷ በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1( ሀ)ና ለ እንዲሁም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 1( ሀ) ፣ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 3 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በህዝብ አስተዳደር ወይም በህዝብ አገልግሎት ላይ በሚፈጸም ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን ÷የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ