አምባሳደር ምስጋኑ ከአዘርባጃን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ፋሪስ ሬዚቨርቨ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ፣ በባለብዙ ወገን እና በሌሎች የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የጋራ የፖለቲካ ምክክሩ ዋና ዓላማ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማሳደግ፣ የትብብር ዋና ዋና መስኮችን መለየት፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ፣ መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከር መሆኑ ተገልጿል ።
አምባሳደር ምስጋኑ የምክክር መድረኩ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን ለማጠናከር እና የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጎልበት ምቹ መድረክ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ፋሪስ ሬዚቨርቨ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር መሰል ምክክር ማድረግና ስምምነቶች መፈራረም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክሩ አዘርባጃን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ መገለፁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል ።