ሃላፊነታቸውን በማይወጡ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተደጋጋሚ ጊዜ በባንኮች እና ሌሎች ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ም/ ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ÷በመዲናዋ በአንዳንድ በግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች የሚቀጠሩ የጥበቃ ሰራተኞች ለፀጥታ አካላት አጋዥ ከመሆን ይልቅ የዘረፋ ወንጀል እንደሚፈጽሙ አንስተዋል፡፡
የጥበቃ ሰራተኞች ከሌሎች ወንጀል ፈፃሚዎች ጋር በመመሳጠር በአንዳንድ ባንኮች ላይ የዘረፋ ወንጀሎች እንዲፈፀሙ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውንም አስረድተዋል፡፡
የከተማው የፀጥታ ስጋት እየሆኑ በመጡ እና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ የግል የጥበቃ ኤጀንሲ እና መሰል ተቋማት ላይ በቅርብ ጊዜ ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
በአንዳንድ ባንኮች ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች የአንዳድ የግል የጥበቃ ኤጀንሲ የጥበቃ ተቀጣሪዎች የሚጠብቁትን ተቋም በመዝረፍም ሆነ በማዘረፍ ዋነኛ ተዋንያን እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች የጥበቃ ሃላፊዎች እና የተቋማቱ ሃላፊዎች ችግሩን ከመፍታት አኳያ ትኩረት ሰጠው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ በመዲናዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በባንኮች ላይ በተለያዩ ስልቶች እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎች አሳሳቢ መሆቸውን ተናግረዋል፡፡
የግል ኤጀንሲዎች የሚቀጥሯቸውን የጥበቃ ሰራተኞች ሕጋዊ ቀጠራ እና ምልመላ ከማድረግ ጀምሮ ክትትል በማድረግና ከፖሊስ አካላት ጋር ጠንካራ የሥራ ትስስር በመፍጠር ሥጋቱን መቀነስ እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል ።