ጥርስ አብቅሎ የተወለደው ሕጻን …
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በዳንግላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንድ የወተት ጥርስ ያበቀለ ሕጻን መወለዱ ተገልጿል፡፡
በሆስፒታሉ አዋላጅ ነርስ የሆኑት መንግስቱ ኤባ በዳንግላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንድ የወተት ጥርስ ያበቀለ ሕጻን መወለዱን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡
መሰል ክስተት ሕጻናት ቀድመው ከ6 ወራት በፊት የወተት ጥርስ የሚያበቅሉበት አጋጣሚ እንደሚፈጠር ሁሉ አዲስ ሕጻናት ሲወለዱም አልፎ አልፎ የወተት ጥርስ አብቅለው የመወለድ እድል እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
ክስተቱ ሲያግጥም በሆስፒታሉ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ አቤ በበኩላቸው ÷ የበቀለው የወተት ጥርስ ለቀጣይ የሕጻኑ ጥርስ አበቃቀል እንዲመች የሚወገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክስተቱ በሕጻኑ ጤና ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው አመልክተዋል፡፡
ማሕበረሰቡም አዲስ በተወለዱ ሕጻናት ላይ መሰል ክስተት አልፎ አልፎ የሚያጋጥም መሆኑን በመረዳት መደናገጥ እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ