ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገ የአየር ብክለት መከላከያ ጋሻችን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ነገ ምግባችን፣ መጠለያ ጥላችን እንዲሁም የነገ የአየር ብክለት መከላከያ ጋሻችን ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ የዛሬዋ ማለዳ ታሪካዊ ናት ብለዋል።
በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ጥሪን ተቀብለን 4 ሚሊየን ችግኞችን በ140 ቦታዎች ከነዋሪዎች ጋር መትከል ጀምረናል ብለዋል።
“ተባብረን ስንሰራ ችግሮቻችን ቀልለው፣ የራቀ የመሰለው ስኬት እየቀረበ በርካቶችን ጠቃሚ ያደረጉ ስራዎችን ሰርተናልም’’ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ውድድሩን ከራሳችን ጋር አድርገን የዛሬውን ስራችንን ከትናንትናው በጥራትም፣ በብዛትም የተሻለ በማድረግ ችግሮቻችንን እየቀደምን የዛሬው ስኬታችን ለተሻለው የነገው ድል እያሻገረን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡
በአንድ ጀንበር በመዲናዋ ከ4 ሚሊየን በላይ ችግኞችን የመትከል መርሐ ግብር ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎችንም አመስግነው፤ ከመትከል በተጨማሪ በመንከባከቡም ተሳትፏቸውን እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ አበባን እየተባበርን በመፍጠር፣ እየፈጠንን ችግሮችን በመርታት ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎቿ የምትመች ውብ ከተማ ለማድረግ በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።