የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ቢሮ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ዋና ዳይሬክተር አቶ መለሰ ኪዊ በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
እቅዱን ለማሳካትም በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን ከመዘርጋት እና ፖሊሲ ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክልሉ ላይ ይስተዋል የነበረው የጸጥታ ችግር ግብር የመሰብሰብ ሒደቱን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ነው ያስረዱት፡፡
በበጀት ዓመቱም ከመደበኛ ግብር ከፋዮች፣ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት እና ሌሎች ዘርፎች 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ተቋማት ውዝፍ ግብር መሰብሰብም ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ