Fana: At a Speed of Life!

 ለአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መንገድ የጠረገው ሕዳሴ ግድብ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ያለውን የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ተፅዕኖ በመቀልበስ ለግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን መሆን መንገድ ጠርጓል አሉ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ ጋሻው አይፈራም (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ አፍሪካ የእምቅ ተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ብትሆንም በቀድሞ ቅኝ ገዥዎች እና ሌሎች ሀገራት ተፅዕኖ ሀብቷ በተገቢው ሊለማ አልቻለም።

አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነጻ ወጥተው ራሳቸውን ማስተዳደር ቢችሉም አሁንም ኢኮኖሚን ጨምሮ ከሌሎች ጉዳዮች ተጽዕኖ መላቀቅ አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም አብዛኛው የአፍሪካ ሀገር በራሱ የገንዘብ ምንጭ እና ፖሊሲ ኢኮኖሚውን መገንባት እንዳልቻለ ጠቅሰው፤ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የሌሎች ጥገኛ ለመሆን መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም አፍሪካውያን ፀጋዎቻቸውን አልምተው እንዳይጠቀሙ በእጅ አዙር ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ እንቅፋቶች እንዲያጋጥሟቸው እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ይህም ኢኮኖሚው እንዳያድግ አድርጓል ያሉት ጋሻው (ዶ/ር)፤ ለአብነትም በማዕድን ሀብቷ በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆነችውን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎንጎን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ካሰበች ብትቆይም በተለያየ ጫና ሀሳቧ እውን ሳይሆን ቆይቶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኩል እውን ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በራስ አቅም ግድቡን እውን ማድረጓ በተለያየ ጫና ውስጥ ሆኖ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል አሳይቷልም ነው ያሉት።

ይህም ለሌሎች ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቀድሞ ዲፕሎማት እና ፖለቲከኛ ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዓባይ ላይ ግድብ የመገንባት ሀሳብ ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን አስታውሰው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል።

ግድቡ ከግድብነት ባለፈ ለኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ከኢትዮጵያውን ለኢትዮጵያውያን የተገነባው ግድቡ የአይቻልም መንፈስን የሰበረ እንዲሁም በርካታ ጫናዎችን በመቋቋም አፍሪካውያን የራሳቸውን ኢኮኖሚ ማልማት እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያሳየ ያለውን ፈጣን እድገት ተከትሎ ለሚመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ተቋማት በቂ ኃይል እንዲያገኙ እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.