Fana: At a Speed of Life!

በአዳማ ከተማ የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የመታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከተማ የተገነባው የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የመታሰቢያ ሐውልት ዛሬ ተመረቀ።

በከተማዋ አሊ ቢራ አደባባይ የተገነባው ሀውልት ምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ትውልዱ ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የዘከረው የህዝቦች አንድነት፣ እኩልነትና ፍቅር ይበልጥ እንዲጎለብት መስራት ይገባዋል ብለዋል።

ትውልዱ እንዲሁም አርቲስቶች በህዝቦች አንድነት፣ መቻቻልና አብሮነት ላይ በቅንጅት በመስራት የአርቲስት አሊ ቢራን ራዕይ ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

አስተማማኝ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲረጋገጥ ብሎም የህዝቦች አንድነት እንዲፀና መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር የአሁኑ ትውልድ ከአርቲስቱ መልካም ተግባር እንዲማርና ራዕዩን እንዲያስቀጥል በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

“አሊ ቢራ ፍቅር፣ አንድነትና እኩልነት ያቀነቀ የነፃነት አባት ነው” ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ ናቸው።

ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ አስተማሪ የጥበብ ስራዎችን ለህዝቡ ማበርከቱን አስታውሰው፤ ለትውልዱ ስንቅ ያስቀመጠ የጥበብ አባት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአሁኑ ትውልድ አሊ በጀመረው መንገድ የህዝቦች አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር እንዲጎለብት መስራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው “ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ አንድነት፣ አብሮነትና ፍቅር የዘከረ ታላቅ አርቲስት ነው “ብለዋል።

“የመታሰቢያ ሐውልት ስናቆም አርቲስት አሊ ቢራ በአስቸጋሪ ወቅት ውስጥ ሆኖ የሰራውን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን ትውልዱ የአርቲስቱን ፈለግ በመከተል ትምህርት እንዲወስድበት ነው” ሲሉ አክለዋል።

ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ የሰራውን ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድና አርቲስቶች ስለ ህዝቦች አንድነት በጥበባቸው መዘከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ሙሐመድ አህመድ ቆቤ በበኩላቸው “ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ህዝብን በማንቃት የነፃነት ድምፅ የሆነ ነው “ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደርና ህዝቡ አሊ ቢራን በሆስፒታል ከመንከባከብ ባለፈ በከተማዋ ጎዳና በመሰየምና የመታሰቢያ ሐውልት በማቆም ትውልዱ ከአሊ እንዲማር ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ ” የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባለቤት ወይዘሮ ሊሊ ማርቆስ ናቸው።

“አሊ ሀገር አለኝ፤ ለሀገሬ በሀገሬ እኖራለው፤ በሀገሬ እሞታለሁ ብሎ ባቀነቀነው ታሪክ ወጣቱ ስለ ሀገር ፍቅር እንዲማር፣ መቻቻልና አብሮነት እንዲጠናከር አድርጓል ” ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.