አምስተኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህልና ቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ ያለመው አምስተኛው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በቱሪዝም ሳምንት መርሐ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የቱሪዝም ሳምንቱ በዋናነት የባህልና ቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅና በባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ትብብርና ትስስር ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
ሁነቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ እየተከናወኑ ላሉት ተግባራት እገዛ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የቱሪዝም ሳምንት መርሐ ግብር ላይ ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት እውቅናና ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን፥ “ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ 2018” እንደምትመረጥ ተጠቁሟል።
በቱሪዝም ሳምንቱ ላይ ከሀገር ውስጥ ባሻገር ከሰባት የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ 27 የሚደርሱ የቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በታምራት ደለሊ