የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙና የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ ሊሆኑ ይገባል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙና የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክሩ ሊሆኑ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዘጋጅነት “መገናኛ ብዙኃን ለአገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለፌደራልና ለክልል የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎችና አርታኢያን ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ መገናኛ ብዙኃን በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲጸናና አንድነት እንዲጠናከር መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
መንግሥት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንደምሰሶ የያዛቸው አቅጣጫዎች ከግብ እንዲደርሱ መገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን በጎ አስተዋጽዖ ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የብዝኃ-ኢኮኖሚው ምሰሶ በሆኑት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይሲቲ ዘርፎች ላይ ትላልቅ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ለአብነትም መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃንም ይህ ዕቅድ ከግብ እንዲደርስ ከማገዝ ባሻገር እውነተኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም መንግሥት ሜካናይዜሽንን በመጠቀም በስንዴ ልማት የሚያከናውነው ውጤታማ ሥራ ላይ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በሌማት ትሩፋትና አረንጓዴ አሻራ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የዘገባዎች ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩም በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተሰሩ ባሉ ተግባራት ዙሪያ በስፋት መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
አካታች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲረጋገጥ መንግሥት እየሰራ ያለውን በጎ ሥራ ሕዝቡ ተገንዝቦ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድሙ ዘገባዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ዘገባዎች አካታች ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን ለምርመራ ጋዜጠኝነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን በዘገባዎቻቸው ለአገር ግንባታ አስተዋጽዖ ለሚያደርጉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በዚህም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ ሚዛናዊ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡