Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች ከአማራ ክልል ጎን እንደሆኑ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ከአማራ ክልል ጎን መሆናቸውን ገለጹ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር በዓለ ሲመት በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሮች ለአዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ፥ ለቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ለክልሉ ላበረከቱት በጎ ሥራ አመስግነዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟት ያውቃል ፤ ሁሉንም እያሸነፈች እዚህ ደርሳለች ፤ አሁን የገጠማትን ፈተናም ታሸንፋለች ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ድል ድላችን ነው ፈተናውም ፈተናችን ነው ፤ ሁሉንም በጋራ እናሳካለን ያሉ ሲሆን ፥ የተሻለችውን ኢትዮጵያ በልጆቿ መሥዋዕትነት ለልጆቻችን እናስረክባለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ፥ በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር በአጭር ጊዜ መሻሻል በማሳያቱ የተሰማቸውን ደስታ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ከገባበት ችግር ወጥቶ ለሀገር ምሳሌ እንደሚሆን እተማመናለሁ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ የሶማሌ ክልል ከአማራ ክልል ጎን መሆኑንም ነው የገለጹት።

የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ፥ የአማራ ችግር የአፋር ችግር ነው ፤ አማራ የሰውነታችን አንድ አካል ነው ፤ አማራ ተረበሸ ማለት ኢትዮጵያ ተረበሸች ማለት ነው ፤ ኢትዮጵያ ስትረበሽ ለጠላት በር እንከፍታለን ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አሉት ፤ ጥያቄዎችን እንዴት እንፍታ የሚለው ነው ወሳኙ ጉዳይም ብለዋል።

ለመሪዎች የመሪነት ዕድል መስጠትና መሪዎችን ማገዝ ችግርን ይፈታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ የአፋር ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከአማራ ሕዝብና መንግሥት ጎን መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ፥ ኢትዮጵያ የሁላችን፤ ሕዝቦቿም የሁላችን ናቸው ፤ ለጋራ ችግሮቻችን በጋራ መሥራት ይገባናል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ጥያቄ ጥያቄያችን ነው፣ የጋራ ችግሮቻችንን በንግግር መፍታት ይገባናልም ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ የብዙ ሺህ ዓመት የመንግሥት ታሪክ ያለው፣ መምራት የሚችል፣ ታጋሽ ፣ ችግሮችን የመፍታት ጥበብ ያለው፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለሀገሩ ቀናዒ፣ ለሀገር አንድነት ክብር ሕይወቱን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ታላቅ ታሪክ ላለው ሕዝብ ችግሮቹን በብልሃትና በንግግር መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ከአማራ ሕዝብና መንግሥት ጎን በጋራ በመቆም ችግሮችን ለመፍታት ኃላፊነት ይዘን እንሄዳለንም ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ፣ ኢ/ር) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር አስታውሰው ፥ አሁን ላይ በጋራ በተሠራው ሥራ ሰላማዊ አየር መተንፈስ ተጀምሯል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ፈተናዎች ሲገጥሙት በጽናት አልፏል ፤ አሁንም የገጠመውን ችግር የመወጣት አቅም አለው፤ የአመራር ጥበብ ያለበት ሕዝብ በመሆኑ ችግሩን ያልፈዋል ብለዋል። ይህን ጥበብና አቅም ከተጠቀምን አሁንም ችግሩን ይፈታል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ እንዲፈቱ እንሠራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ፥ አሁን ላይ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የተሻለ አውድ መኖሩንም አንስተዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የሚቻለውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡመድ ዑጅሉ የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ እንፈታለን ብለው ፥ ጠላቶቻችን በየጊዜው አጀንዳ እየሰጡ ከግጭት አዙሪት እንዳንወጣ አድርገዋል ነው ያሉት።

ችግሮቻችን የጋራ መሆናቸውን በማሰብ በጋራ መሥራት ይገባል ፤ የጋምቤላ ክልልም የአማራ ሕዝብ ወደ ሰላም እንዲመለስ አብሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ ፈትተን በጋራ እንሻገራለን ሲሉም ነው የገለጹት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ የአማራ ሕዝብ የጀግንነት ድል በክብር የሚያከብር ሕዝብ በጥቂት ችግር አይንበረከክም ብለዋል፡፡

ከአባቶቻችን የወሰድነውን ጽናት ዛሬ ላይ መውሰድ ከቻልን ፤ ፈጣሪን ከፈራን እና ከተከባበርን ችግሮቻችን ይፈታሉ ሲሉም ነው የተናገሩት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከአማራ ክልል ጎን እንደሚቆምም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ፥ እጅና ጓንት ሆነን ከሠራን ችግሮችን በአጭር ጊዜ እንፈታለን ብለዋል፡፡

ለሚከሰቱ ችግሮች ፈጥኖ መፍትሔ መስጠት ይገባል ብለውም ፥ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ከአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ጋር እንደሚቆም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.