በመቀሌ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራ መጀመሩን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የመቀሌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ የመሠረተ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ሶሎሞን ገብረ-ሚካዔል(ኢ/ር) ÷ የመሠረተ ልማት ግንባታው በመንገድ ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በበጀቱ የ66 ኪሎ ሜትር ነባር የውስጥ ለውስጥ የጠጠር መንገድ ግንባታ የማጠናቀቅ ሥራ ፣ የ83 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዳር የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታዎች እንደሚከናውኑም ተናግረዋል።
በመቀሌ ጎዳና የልዩ መብራት ተከላ ለማካሄድም የኤሌክትሪክ መሥመር ዝርጋታ ሥራ እንደሚካሄድ ጨምረው ጨምረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማቶች ግንባታና ዝርጋታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።
የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን በ10 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን አመላክተዋል።
የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ህብረተሰቡን በባለቤትነት ባሳተፈ መልኩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ኃላፊው አስታውቀዋል።