በትውልዶች መካከል የእውቀት እና የልምድ ልውውጥ የማይናቅ ጠቀሜታ አለው -ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትውልዶች መካከል የእውቀት እና የልምድ ልውውጥ የማይናቅ ጠቀሜታ አለው ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
የትውልድ ቀን ‘ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር’ በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ እየተከበረ ነው።
በዚህ ወቅትፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ÷ የአሁኑ ትውልድ እራሱን ሊጠይቅ የሚገባው ለቀጣይ ትውልድ የማስተላልፈው ምንድነው የሚለውን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በሚደረገው ሁሉ ዛሬን ብቻ ፣ የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን ተተኪውን ተውልድ ያገናዘበ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡
ወጣቶች ተደራጅተው የሚነጋገሩበት መድረክ መኖር እንዳለበት በማንሳትም አንድ ላይ መነጋገር የማሰብ ሃይል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት የተቀረጠ ሳይሆን ሰንሰለት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ትውልዱ የራሱ የሆነ ችግሮች እንዲሁም አመቺ ሁኔታዎችን የሚያልፍ መሆኑንም አስረድተዋል።
“ቀላሉ ድምዳሜ ችግርን፣ ጥፋትን ፣ያልሆኑ ነገሮችን ፣ ተጠያቂነቱን ሁሉ የቀድሞው ትውልድ ላይ መጣል፣ ያለፈውን መውቀስ የአሁኑ ወጣት ደግሞ ብዙም ሳይሰራ ማወደስ የሚለው ላይ ሚዛናዊ የሆነ አካሄድ ሲኖረን ነው ትውልድን ሽግግር በጥሩ ሁኔታ እንዲኖር የምናደርገው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በተለይ መወቃቀስ ሳይሆን የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ፡፡
ሌላው ትውልድን ሊያንፅ ከሚችል ነገር አንዱ ማንበብ መመራመር ነው፤ይህም ተተኪው ትውልድ የመሞገት መንፈስ እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡
ይህም ሁሉንም አሜን ብሎ ሳይሆን አውቆ ይቀበላል፤ለዚህም የማንበብ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ መሸጋገር ያለበት እሴት ሃቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ታታሪነት እና ሀገር ወዳድነት ይገኝበታል ብለዋል፡፡
መጪው ልውልድ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉት የተቆሙት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ የአሁኑ ትውልድ እውቀት እና ክህሎት እያለው ሀገር ማገልገል ላይ መላላት እንደሚስተዋልበት አንስተዋል።
ትውልዱ ልዩነት በጦርነት የማይፈታ መሆኑን የሚያምን መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው