የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ ሙሌት መጠናቀቅ አስመልክቶ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ምን አሉ ?
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ደረጃ አከራካሪ ሆኖ የቆየው በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በሥኬት መሞላቱን ኢትዮጵያ ካስታወቀች በኋላ ግብፅ ቁጣዋን ማሰማቷን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቢቢሲ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ያፈሰሰችበት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የእናንተን የውሃ ድርሻ አይነካም እያለች ስታስረዳ ብትቆይም ግብፅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል “ኢትዮጵያ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ንቃለች” ማለቷን ነው ያስነበበው፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክንያት ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር እሠጥ-አገባ ውስጥ ቆይታለችም ነው ያለው ዘገባው፡፡
የጀርመን ድምጽ ሬዲዮም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ÷ “የሕዳሴው ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው ዙር ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ሳበስር በታላቅ ደስታ ነው” ማለታቸውን ገልጾ ፕሮጀክቱ “ውስጣዊ እና ውጫዊ መሰናክሎች” እንዳጋጠሙት መናገራቸውንም አትቷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቷን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በእጥፍ ሊያሳድገው እና የአፍሪካ ትልቁ ግድብ ሊሆን ነው ሲልም የፕሮጀክቱን ታላቅነት ገልጾታል፡፡
ኢትዮጵያ በአወዛጋቢው የዓባይ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አዲስ ምዕራፍ አበሰረች በማለት የዘገበው ደግሞ ስካይ ኒውስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሙሌቱን የመጨረሻ ዙር መጠናቀቅ ያበሰረችለት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት በአንድ ወቅት የግብፅ ፖለቲከኞች ወታደራዊ እርምጃ እንወስዳለን እያሉ ሲዝቱበት የነበረው ነው በማለትም ነው ያስታወሰው፡፡
ግድቡ ከ6 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የኃይል ማማ ለመሆን የምታደርገው ጥረት አንድ አካል አድርጋ እንደምትመለከተውም ጠቁሟል፡፡
ኦል አፍሪካ ዶት ኮም በበኩሉ ኢትዮጵያ የታላቁን ግድቧን የውሃ ማጠራቀሚያ ሙሌት አጠናቀቀች ሲል አስነብቧል።
በሌላ በኩል ኢጂፕት ኢንዲፔንደንት ÷ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጨረሻው ዙር ሙሌት የሥምምነት መርሆዎችን እንደሚጥስ ግብፅ ጠቅሳ መውቀሷን ዘግቧል፡፡
ግዙፉ ፕሮጀክት የዓባይን ወንዝ ፍሰት ይቀንስብኛል ብላ ሙሌቱን አጥብቃ እንደምትቃወምም ነው ዘገባው ያስነበበው።
ዘ ሪዮ ታይምስ ደግሞ ÷ “ኢትዮጵያ ግድቡን ሞላች” ሲል ፅፏል፡፡
በዓለማየሁ ገረመው