Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰራት እንዳለበት ተጠቆመ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የድህረ-ምርት ብክነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ በአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽነር ጆሴፋ ሳኮ ገለጹ።

4ኛው የመላ አፍሪካ የድህረ-ምርት ጉባዔና አውደ ርዕይ ‘ዘላቂ የድህረ-ምርት አስተዳደር በአፍሪካ የግብርና ንግድ ማሳደግ፣ የምግብ ደኅንነትና የተመጣጠነ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መካሄድ ጀምሯል።

ኮሚሽነር ጆሴፋ ሳኮ በወቅቱ እንደገለጹት÷ የምርት ብክነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነስና ሌሎች ጉዳዮች በአህጉሪቱ ህዝብ የምግብ ደህንነት ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው።

ጉባዔው የምርት ብክነትን ጨምሮ በግብርና ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ በተቀናጀ መልኩ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መፍትሔ ላይ ለመምከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህረ ምርት ወቅት 800 ሚሊየን ዜጎችን መመገብ የሚያስችል ምርት እንደሚባክን ጠቅሰው÷ በአፍሪካም ከሚመረተው ሰብል 30 ከመቶ በላይ እንደሚባክን ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ800 ሚሊየን በላይ እንዲሁም በአፍሪካ 278 ሚሊየን የርሃብ አደጋ ያጋጥማልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት አህጉራዊ ቢሮ ረዳት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አበበ ኃይሌ÷ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የድህረ-ምርት ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፉ የሃብት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተርና ምክትል ፕሬዚደንት ዋንጂራ ማታይ በበኩላቸው÷ በአፍሪካ የእርስ በርስ የግብርና ምርት ንግድን በማሳደግ የምግብ ደህንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በጉባዔው የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.