በሰሜን ጎንደር ዞን ከ200 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሀላፊ ይርዳው ሲሳይ እንደገለጹት÷ በዞኑ በድርቅ ምክንያት 452 ሺህ 851 ሰዎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
ከዚህ ውስጥ 202 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
በድርቁ ምክንያት 19 ሺህ 174 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ማሳ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
በእንስሳት ላይም ተመሳሳይ ጉዳት እየደረሰ ሲሆን÷ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማዘዋወር ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡
በበየዳ፣ ጠለምትና ጃናሞራ 4 ሺህ 88 ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው መሄዳቸውንም ነው ሀላፊው የተናገሩት።
በችግሩ ምክንያት የተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ መከሰቱን ጠቅሰው÷ ሁሉም አካል የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰላም አስመላሽ