በባሕር ዳር ሁለት አካባቢዎች በመኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ የእሳት አደጋ ደረሰ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 9 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሕር ዳር ሁለት አካባቢዎች ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በመኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ የደረሰ የእሳት አደጋ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከተለ፡፡
አደጋው የደረሰው ቀበሌ 8 በሚገኝ የመኖሪያ ቤት እና ቀበሌ 12 አካባቢ በሚገኙ የሞባይል መሸጫ የገበያ ማዕከላት ላይ ነው፡፡
ቀበሌ 8 ከሌሊቱ 5፡50 አካባቢ ከአንድ መኖሪያ ቤት የተነሳ እሳት መኖሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲወድምና ከጎረቤት ያለ ሌላ ቤት ላይ መጠነኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
የእሳት አደጋው በመኖሪያ ቤቶቹና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በቀር በሰው ሕይወትም ሆነ በአካል ላይ ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በቀበሌ 12 በሚገኘው የሞባይል የገበያ ማዕከል ላይም የእሳት ቃጠሎ የደረሰ ሲሆን በአደጋውም 48 ሱቆች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙሁለት የገበያ ማዕከላት ባሉት የሞባይል የገበያ ማዕከል የተነሳው እሳት ሁሉንም ሱቆችና በውስጣቸው የነበረውን ንብረት ማውደሙ ተነግሯል፡፡
ወጣቶች፣ የፀጥታ ኃይል አባላት፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ መኪና ደርሰው ወደ ሌሎች ሱቆችና ድርጅቶች ሳይስፋፋ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን አብመድ ዘግቧል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ታደሰ ዳኛቸውም የአደጋው መንስኤ እየተጣራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡