የተሰጠን ኃላፊነት በእውነት፣ በትጋት እና በቅንነት በማገልገል ህዝባችንን እንክሳለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሰጠን ኃላፊነት በእውነት፣ በትጋት እና በቅንነት በማገልገል ህዝባችንን እንክሳለን አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የከተማችን ባለሀብቶች ፓርቲያችን ብልፅግና ሀገራችንን ለመገንባትና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ እየተጋ መሆኑን ገብቷችሁ፣ ግልፅ አቋም ይዛችሁ፣ በሁሉም መልኩ በንቃት በመሣተፍ ላደረጋችሁት ድጋፍ ሁሉ በድጋሚ እናመሰግናለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ የአንድ ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ከማግኘት በላይ ከፍ ያለ ሀገርን የማፅናት ተግባር ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ህዝባችን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያሳየውን ፅናት፣ የተጀመረው የሀገር ልማት ለማስቀጠል ያለውን ፍላጐት እና ሰላምን ዘላቂ የማድረግ ጉዞ እንዲሳካ ለፓርቲያችን ዳግም ታላቅ ኃላፊነትና አደራ ተሰጥቷል ሲሉም ተናግረዋል።
በተሰጠን ኃላፊነት በእውነት፣ በትጋት እና በቅንነት በማገልገል ህዝባችንን እንክሳለን ነው ያሉት።
ፓርቲው በግሉ ሴክተር ጠንካራ አጋርነት ብልፅግና ይረጋገጣል ብሎ እንደሚያምን ጠቅሰው፤ ለዚህም የግሉ ሴክተር ለሀገር ግንባታ በምታደርጉት ጥረት ሁሌም ድጋፋችን አይለያችሁምና በትብብር መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡