የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የግምገማ መድረክ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ሀላፊዎች የሚሳተፉበት የግምገማ መድረክ በባህር ዳር መካሄድ ጀመረ፡፡
በመድረኩ በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች እንዲሁም የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ ላይ ምክክር ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ÷ በግጭት ምክንያት የወደሙ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትንና የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ከመልካም አስተዳደር አኳያ በተለይ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ከአመራሩ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም መገንባት የክልሉ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የሚሳተፉበት የግምገማ መድረክ ባህር ዳርን ጨምሮ በጎንደር፣ በደሴና በደብረ ብርሐን ከተሞች እንደሚካሄድ መግለጻቸውን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡