አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር ተወያይተዋል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀበሉትን መልዕክት ለፕሬዚዳንቱ አድርሰዋል።
በውይይታቸው ወቅት፥ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሁለትዮሽ፣ በባለብዙ ወገንና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚያስችል ጉዳይ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
ሀገራቱን በመሰረት ልማት ለማስተሳሰር ጠንካራ የትብብር ስራ ለመስራት ሁለቱ መሪዎች ከስምምነት መድረሳቸውም ነው የተገለጸው።
በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር የነበራቸውን ውይይት ከጨረሱ በኋላ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ሞርጋን ጋር በመሆን የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።