ከ9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ከተለያዩ የሃይል ምንጮች ከ9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ተችሏል አለ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ከተለያዩ የሃይል ምንጮች የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ሃይል ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም በከተማና ገጠር የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ይበልጥ በማጠናከር ዜጎችን የሃይል ተጠቃሚ ማድረግ ላይ በቁርጠኝነት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የሃይል ምንጮች የመነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል ከ7 ሺህ 910 ሜጋ ዋት ወደ 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ከውሃ ሃይል 9 ሺህ 201 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ ሃይል 504 ሜጋ ዋት፣ ከጸሐይ ሃይል 15 ነጥብ 32 ሜጋ ዋት፣ ከደረቅ ቆሻሻ 25 ሜጋ ዋት እና ከከርሰ ምድር ሙቀት ሃይል 7 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ከብሔራዊ ግሪድ 490 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ በማድረግ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር 5 ነጥብ 82 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
በሌላ በኩል ከብሔራዊ ግሪድ ውጪ ተጨማሪ 8 ሺህ 910 ደንበኞችን ተጠቃሚ በማድረግ 18 ሺህ 73 ደንበኞችን የኦፍ ግሪድ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከነበረበት 52 በመቶ ወደ 54 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ 53 በመቶ ማድረስ መቻሉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ