ሃገር አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎች ውድድር መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 8ኛው ሃገር አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎች ውድድር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት መሪ አስፈፃሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር)፥ የፈጠራ ስራ የዛሬን ውጤት ብቻ ያለመ ሳይሆን ለቀጣይ የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ዛሬ አድገው የምናያቸው ሀገራት የደረሱበት እድገት ዋናው ሚስጥር ሳይንስ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የስቲም ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሮ አሰገደች ሻውል በበኩላቸው፥የሳይንስ ትምህርትን በተግባር አስደግፎ በማስተማርና ከትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የፈጠራ ስራዎቸን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ስራዎች ውድድር 211 ችግር ፈች የፈጠራ ስራዎች እንደቀረቡ መገለጹን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የተማሪዎች የፈጠራ ስራ ውድድር አውደ ርዕይ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተጠቅሷል፡፡