Fana: At a Speed of Life!

ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሥምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከዓለም አቀፉ የሙዚቃ ኩባንያ ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ (UMG) ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሥምምነቱ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያንን በዓለም አቀፉ የሙዚቃ ገበያ ላይ ለማስቀመጥ እንደሚያግዝ ሰዋሰው መልቲሚዲያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ የሚንፀባረቁ ባህሎችን ለቀሪው ዓለም ለማሳየት ያስችላልም ነው የተባለው።

በሥምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያውያኑን ስራ ከማስተዋወቅ ባለፈ በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ የተዘጋጁ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድምፃውያን ሙዚቃዎች በሰዋሰው መተግበሪያ ላይ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይሆናሉ ተብሏል።

ሰዋሰው መልቲሚዲያ ከአንድ አመት በፊት የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ የተቀላቀለ ሲሆን፥ ድምፃውያን፣ ገጣሚያን፣ የዜማ ደራሲዎች እና አቀናባሪዎችን ስራዎች በማዘጋጀት እያቀረበ ይገኛል።

ይህንን የባለሙያዎች ስራም በሰዋሰው መተግበሪያ አማካኝነት ለህዝብ እያደረሰ እንደሚገኝም ነው የገለጸው።

ዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ግሩፕ የመዝናኛውን ኢንዱስትሪ በ1930ዎቹ የተቀላቀለ ሲሆን፥ አሁንላይ ከ46 ቢሊየን ዶላር በላይ በማንቀሳቀስ የዓለምን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በቀዳሚነት ይመራል።

ስመ ጥር ዓለም አቀፍ ድምፃውያንን የያዘው ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አዲስ አብዮትን ለመፍጠር በመስራት ላይ ከሚገኘውና አንጋፋ ድምፃውያንን እና ሙዚቀኞችን ከያዘው ሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር በጥምረት የሚሰራ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.