ፕሮጀክቶች በጥራትና በጊዜ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ክትትል ማድረጋችንን እንቀጥላለን – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ክትትል እያደረግን ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማ መገንባታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ÷ በመዲናዋ እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘመናዊ የትራስፖርት ማዕከል፣ የየካ መኪና ማቆሚያና አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከልን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም የግንባታ ሂደታቸውን እንደገመገሙ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
በዚህም ዘመናዊ የትራስፖርት ማዕከል 63 በመቶ፣ የየካ መኪና ማቆሚያ 66 በመቶ እንዲሁም አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል 85 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት፡፡
“የህዝብ ሃብትን በቁጠባ በማስተዳደር በጥናት ላይ ተመርኩዘን ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የጀመርናቸው ፕሮጀክቶቻችን በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
በዚህም ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማ መገንባታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡